በመቀለ የተፈፀመው የድሮን ጥቃት "የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል" ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, HRW
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በትግራይ ክልል በመኖሪያ ግቢ ላይ የተፈፀመው የድሮን ጥቃት "የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል" ተቆጥሮ ሊመረመር እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ።
ሂውማን ራይትስ ዎች ነሐሴ 14፣ 2018 ዓ.ም ተፈፀመ ባለው ጥቃት ሰባት ሕፃናትን ጨምሮ 13 ሰላማዊ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቅሷል።
የመብት ተሟጋች ተቋሙ ትናንት አርብ መስከረም 15፣ 2019 ዓ.ም. አመሻሽ ባወጣው መግለጫ የአየር ጥቃቱ በክልሉ መቀመጫ መቀለ ዳእሮ በተባለ ሰፈር ምንም ዓይነት ወታደራዊ ዒላማ በሌለበት ቦታ መፈፀሙን አመልክቶ፣ ጥቃቱ "ሕገወጥ" እና "ማንንም ያልለየ" እንደሆነ ገልጿል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በገለልተኛ እና ግልጽ በሆነ መንገድ ጥቃቱን መመርመር እንዲሁም በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉትን ለሕግ ማቅረብ እና ለተጎጂዎች በቂ ካሳ መክፈል አለባቸው ብሏል።
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በመቀለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸመ ድሮን ጥቃት ከ13 ሰዎች በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጾ፣ ለጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱን ተጠያቂ አድርጓል።
በአይደር ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል አስተባባሪ ብርሃኑ ኃይለማሪያም በድሮን ጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው 14 ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን እና "ሦስት ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው" ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥቱም ሆነ ከመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ ተፈጸመ ስለተበላው የድሮን ጥቃት ያሉት ነገር የለም።
በሰሜን ኢትዮጵያ ተቀስቅሶ የነበረው ደም አፋሳሹ ጦርነት ከአራት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋነይት ከቆመ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ያለው ቁርሾ እየተካረረ መጥቶ ረቡዕ ዕለት በይፋ ዳግም ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
ህወሓት "ከፌዴራል ኃይሎች ተፈፀመብኝ" ያለውን ጥቃት ለመከላከል ግጭት ውስጥ መግባቱን የጠቀሰ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱም ከህወሓት ለተከፈተበት ጥቃት የመከላከያ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።
የአሁኑ ግጭት በይፋ የተጀመረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች " የፌደራል መንግሥቱን ከሥልጣን ለማውረድ" ጥምረት መፍጠራቸውን ባስታወቁ ማግስት ነው።
በአማራ እና አፋር አዋሳኝ ቦታዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። በአማራ ክልል ታሪካዊ ቅርስ መገኛ በሆነችው ላሊበላም ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ሐሙስ ዕለትም ወደ ከተማ የሚደረገው በረራ መቆሙን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች እና በደቡብ ትግራይ ፈፀመ ያሉትን ጥቃት እና በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን አውግዘው የግጭቱ መባባስ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ወትሮም ከጦርነት ያላገገመው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አሁን የተቀሰቀሰው ግጭት የሚደርሰውን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ይበልጥ ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ሌቲሽያ ባደር "በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት ሕገ ወጥ ጥቃቶችን እንዲሁም የሲቪሎች ደኅንነት በተመለከተ ያለውን ስጋት ያባብሳል" ብለዋል።
በመሆኑም በሲቪሎች ላይ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርስ ለመከላከል የኢትዮጵያ ጦር የጦርነት ሕጎችን እንዲያከብር እና ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ሁሉንም ተጨባጭ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
ከነሐሴ 11 እስከ ጳጉሜ 1፣ 2018 ዓ.ም. ድረስ ከዳዕሮ ጥቃት የተረፉ ግለሰቦች፣ ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች እና ሁለት ነዋሪዎችን ማነጋገሩን እንዲሁም የሳተላይት ምሥሎችን፣ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን እንዳጣራ የገለጸው ተቋሙ፣ በዳዕሮ መኖሪያ ግቢ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ክስተቱን በተመለከተ የኢትዮጵያን ጦር ቃል አቀባይ ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ይህ የድሮን ጥቃት በተፈፀመ በዚያው ዕለት በመቀለ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ኩዊሃ በተባለ ሰፈር ለወታደራዊ ዓላማ ይውል በነበረ ቦታ ላይ ሁለተኛው የአየር ጥቃት መፈፀሙን ተቋሙ ገልጿል። በዚህ ጥቃት ግን የደረሰ ጉዳት አልተገለጸም።
እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል እንደገና ግጭት ባገረሸበት ወቅት ነው።
ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ በፌደራል ኃይሎች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሱዳን ድንበር አካባቢ የተቀሰቀሰው ግጭት እንደቀጠለ ነው። የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እርምጃዎች የፌደራል መንግሥቱ በርካታ የአየር ድብደባዎችን እንዲፈፅም ማድረጋቸውን እና የሲቪል ጉዳቶችን እንዳስከተሉ ተቋሙ ገልጿል።
ሰኞ መስከረም 11፣ 2019 ዓ.ም በትግራይ የእርዳታ መኪና ላይ የድሮን ጥቃት የተፈፀመ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት እርምጃውን አውግዟል።
ከቀናት በፊትም የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ በረራዎች የተቋረጡ ሲሆን ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ይበልጥ ሊስፋፋ ይችላል በሚል ተሰግቷል።



































